የታሰሩት ጋዜጠኞች ቁጥር 18 ደርሷል

በኢትዮጵያ ውስጥ ከቀን ወደ ቀን ለእስር የሚዳረጉ ጋዜጠኞችና ምሁራን ቁጥር እየበረከተ መጥቶ በቅርቡ ተይዘው የታሰሩትን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር 18 መድረሱ እንዳሳሰበው ዓለም አቀፉ የፀሐፊና እስረኞች ኮሚቴ ፔን ገለፀ።

ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን የቀድሞው ሳምንታዊው ኢትኦጵ ጋዜጣ ዋጋ አዘጋጅ በአዲስ ዜና ጋዜጣ ላይ ሲሰራ ተይዞ የታሰረው እ.ኤ.አ ህዳር 9 ቀን 2005 ሲሆን የተከሰበት ወንጀል ስም መጥፋት እንደሆነ ያመለከተው ኮሚቴው ስምንት ወር ተፈርዶበት ወህኒ መውረዱን ጠቅሷል። ወሰንሰገድ የቀድሞው ዲፕሎማት ሀብተማሪያም ስዩምን በተመለከተ የኢትኦጵ ጋዜጣ አዘጋጅ እያለ ባሳተመው ጽሑፍ ምክንያት ነው።

ጌታቸው ስሜ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሲሆን ሦስት ወር ተፈርዶበት ወህኒ ወርዷል። ጋዜጠኛ ጌታቸው ስሜ ተከሶ ወህኒ የወረደው የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ኮፒ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር በወቅቱ አላደረስክም በሚል ምክንያት መሆኑ ታውቋል። የዳግም ወንጭፍ ጋዜጣ አሳታሚ አቶ ለይኩን እንግዳ 15 ወር እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ ይገኛሉ። ለአቶ ለይኩን መከሰስ ወንጀል ሆኖ የቀረበው «የተዛባ ዜና አትመሃል» የሚል ነው። የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጣ አዘጋጅ መለሰ ገስጥም ባለፈው ዓርብ ተይዞ መታሰሩ ታውቋል።

የሀዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና ምክትል ዋና አዘጋጅ የሆኑት ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደና ፈለቀ ጥበቡ በእስር ላይ ይገኛሉ። የነፃነት ጋዜጣ አሳታሚ ዘካሪያስ ተስፋዬና የጋዜጣው ምክትል ዋና አዘጋጅ ደረጀ ሀ/ወልድ በእስር ላይ ይገኛሉ። የአዲስ ዜና ጋዜጣ አሳታሚ ፋሲል የኔዓለም የኢትኦጵ ጋዜጣ አስታሚ አቶ ሲሳይ አጌና፣ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አንዱዓለም አየለ፣ የሳተናው ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ናርዶስ መአዛ በምኒልክ ጋዜጣ ወርቅ ሰገድ ዘለቀ ከአስኳል ጋዜጣ ዳዊት ፋሲል በእስር ላይ ይገኛሉ። የሚኒሊክ፣ ሳተናው እና አስኳል ጋዜጦች አስታሚ ሠርካለም ፋሲልና አቶ እስክንድር ነጋም በእስር ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኞችና ምሁራን እስር እጅግ እንዳሳሰበው ኮሚቴው ገልጾ መንግሥት በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈታቸው ጠይቋል።

ከጦማር ታኅሣሥ 12 ቀን 1998

ሰለ እዚህ ዜና ዋርካ ስር በአማርኛ ይወያዩ !