የሰኔ 1 ግድያና አመጽ በውጭ መርማሪዎች እንዲጣራ ተጠየቀ

በአዲስ አበባ ሰኔ 1 ቀን የተፈፀመው ግድያና አመፅ ላይ እስካሁን ምርመራ አለመካሄዱ ግራ እንደሚያጋባ የገለፁት የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ክሪስ ስሚዝ፣ የውጭ አገር ባለሙያዎች የተካተቱበት ምርመራ በአስቸኳይ እንዲጀመር ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለምልልስ ጠየቁ።

መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከማዋከብ እንዲታቀብ ያሳሰቡ ሲሆን፤ ተቃዋሚዎችም ፓርላማ ገብተው እንዲሳተፉ በመምከር፣ ሁሉም ወገን አመፅ እንደማያዋጣ ማወቅ አለበት ብለዋል - በኮንግረስ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስ ስሚዝ።

የሰኔ 1 ግድያ «በመንግሥት ስፖንሰር የተደረገ አመፅ» እንደሆነ በመግለፅ በማግስቱ ለጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የተቃውሞ ደብዳቤ የፃፉት ክሪስ ስሚዝ፣ እስካሁን ምርመራ አለመካሄዱ አሳሳቢ እንደሆነ ሰሞኑን አዲስ አበባን ሲጐበኙ ገልፀዋል።

ከአቶ መለስ ጋር ተገናኝተው ሲወያዩ፣ በምርጫው የውጭ ባለሙያዎች እንዲካተቱ ሀሳብ አቅርበው እንደሆነ ተጠይቀውም፤ ከውይይቱ በኋላ የመጣላቸው ሃሳብ እንደሆነ ተናግረዋል።

ምርመራው ተአማኒነት እንዲያገኝ የውጭ ባለሙያዎች ተሳትፎ ጠቃሚ እንደሆነ ክሪስ ስሚዝ ጠቁመው፤ የግድያው ተጠያቂዎች በፍ/ቤት ተዳኝተው ወህኒ መውረድ አለባቸው ብለዋል።

ግድያው «በመንግሥት ስፖንሰር የተደረገ አመፅ» እንደሆነ መናገራቸውን በተመለከተም፤ «እንዲህ ብሎ መናገር ግድየለሽነት ይሆብኛል» ካሉ በኋላ፤ የግል አስተያየታቸውን በግል ይዘው እንደሚቆዩና ምርመራውን እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።

ስለምርጫው አቤቱታዎች በገለልተኛ አካል እንዲጣራና እንዲደገም በተቃዋሚዎች ስለቀረበው ሃሳብ ሲናገሩም፣ ምርጫው ቀላል የማይባሉ ስህተቶች ስለተፈፀሙበት የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ እንዳልተደሰቱበት በመጥቀስ፣ የስህተቱን መጠን ለማወቅም ሆነ የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ በያዝነው ወር በውጭ ታዛቢዎች ይፋ የሚደረገውን ሰፊ ሪፖርት ማየት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል - ክሪስ ስሚዝ።

የአውሮፓ ሕብረት ያካሄደው መረጃን የመሰብሰብ ስራ ኢህአዴግ መሸነፉን ያሳያል በማለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደነገሯቸው ክሪስ ስሚዝ አስታውሰው፤ መረጃው የተሰበሰበው ከ38 ሺ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ1 ሺ ብቻ እንደሆነና የመላ አገሪቱን ውጤት እንደማይወክል የአውሮፓ ህብረት ሰዎች እንደጠቆሟቸው ገልፀዋል።

በመረጃው መሰረት ተቃዋሚዎች 47 በመቶ፣ ኢህአዴግ 39 በመቶ ድምጽ ማግኘቱ እንደተዘገበ ይታወሳል።

በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ብቻ ግፊት እንዳላደረጉ የተናገሩት ክሪስ ስሚዝ፣ በፓርላማ ክርክር ተሳታፊ በመሆን አዎንታዊ ስኬት ሊያገኙ እንደሚችሉ መናገራቸውን አልካዱም። የምርጫ ውጤት ላይ የሚነሳ ተቃውሞ ከአመፅ የፀዳ እንዲሆን፣ መንግሥት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በፖሊስ መከታተሉንና ማስፈራራቱን እንዲያቆም በግልፅ አሳስቤያለሁ ብለዋል ክሪስ ስሚዝ።

ከአዲስ አድማስ ነሐሴ 14 ቀን 1997

ሰለ እዚህ ዜና ዋርካ ስር በአማርኛ ይወያዩ !